የሎቄ ሰማዕታት ቀን 16ኛ አመት አከባበርን በተመለከተ ከሲዳማ ኤጄቶ የተሰጠ መግለጫ

በትላንትናው ዕለት በአገር ውስጥና በውጪ የሚኖሩ የሲዳማ ብሔር ተወላጆችና ሲዳማን የሚወዱ ሌሎች ኢትዮጵያውያን በግንቦት 16/1994 ዓ/ም በጭካኔ የተገደሉ ወገኖቻችንን በተለያየ መልኩ በማስታወስ ውለዋል። በተለያዩ ዪንቨርሲቲወችና በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች  የሚማሩ ተማሪወች፥  ነጋዴወች፥  በተለያየ የሙያ መስክ የተሠማሩ የሲዳማ ኤጄቶወችና የተቀረው የሲዳማ ሕዝብ በሙሉ የትላንትናውን ቀን ለማስታወስ ካደረጉአቸው ነገሮች ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው። በያሉበት ጥቁር ልብስ በመልበስ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን ሀዘናቸውን ገልጸዋል፤ የተገደሉ ወገኖችንን ፎቶ በመያዝ  የህሊና ጸሎት በማድረግና ጧፍ የማብራት ሥነስርዓት  በማካሄድ በህይወት ለለሉ ወገኖች የመንፈስ አንድነታቸውን ገልጸዋል፤ የሟቾቹን ቤተሰቦችን ጎብኝተዋል እርዳታም አድርገዋል፤ እጃቸውን  ወደ ላይ በማንሳትና በማጣመር የሟቾቹን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የሀሳብ አንድነታቸውን አመልክተዋል፤ በተለያየ መልኩ የፌስ ቡክ ፕሮፋይል ፎቶአቸውን ስለጭፍጨፋው በሚገልጽ ፎቶ በመቀየር ሃዘናቸውን ገልጸዋል፤ የተለያዩ ቪድዮወችን በመስራትና ጽሁፎችን አሳትሞ በማሰራጨት  የሎቄ ሰማዕታት የተሠውለትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ አንድነታቸውንና  ቁርጠኝነታቸውን ስገልጹ ውለዋል።

የሲዳማን ህዝብ የማንነት ጥያቄ አንግበው ህገመንግሥቱን ተከትለው የወጡ ንጹሓን ዜጎች ላይ ጨካኝ የሆኑ የደኢህዴ/ህወኃት አመራሮች የወሰዱባቸው የግፍ ጭፍጨፋ  የሲዳማ ህዝብ ለነጻነቱና ለማንነቱ የሚያደርገውን ትግል አጠናከረው እንጅ ለአፍታም ያህል ትግሉን በምንም መልኩ አልገታውም። ሆኖም ግን እነዚህ ንጹሐን ወንድሞቻችን የሞቱበት ዓላማ እርሱም የሲዳማ ህዝብ እራስን በራስ የማስተዳደር የማንነት ህገመንግሥታዊ ጥያቄ ሳይመለስ በተለያየ መልኩ ስታፈን ዛሬ 16 ዓመታት አልፈዋል። ንጹሐን ዜጎቻችንን ቃለጉባኤ በመያዝ ለየት ባለ የጦር ሜዳ መሣርያ እንድገደሉ ትዕዛዝ በመስጠት ያስጨፈጨፉ ግለሰቦች እስከ ዛሬ ድረስ  ህግ ፊት ቀርበው ተገቢውን ፍርድ አልተቀበሉም። በመሆኑም እስከ ዛሬ በዚህ የጅምላ ጭፍጨፋ ነፍሳቸውን ያጡ ዜጎቻችንና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም መላው የሲዳማ ህዝብ ፍትህ አላገኘም። የሟች በተሰቦች፣ በዚህ ግፍ ምክንያት ለተለያዩ  የአካል ጉዳት የተዳረጉና ለስነልቦና ችግሮች የተዳረጉ ግለሠቦች ተገቢውን ካሣ አልተቀበሉም።

አሁን ሁላችንም እንደሚናውቀው በአገራችን የተፈጠረውን የለውጥ ጭላንጭል በመጠቀምና ከአዲሱ ጠቅላይ ሚንስቴር ጎን በመቆም የሲዳማ ኤጄቶወች ለዘመናት በክፉ መሪዎች ታፍኖ  የቆየውን የንጽሓን የሲዳማ ተወላጆች ውድ ዋጋ  የከፈለበትን ትግል በተቀናጀ፥ በተደራጀና በተጠናከረ መልኩ በማካሄድ ላይ ይገኛል። ይህ ትግል የሲዳማ  ክልል የመሆን ጥያቄ እስክመለስ፥ የሲዳማ ህዝብ ለጥቅሙ የሚሠራውን ህገመንግሥታዊ በሆነ መልኩ በነጻነት  እስክመርጥ፥ ዲሞክራሲ እስክሰፈንና የህግ የበላይነት እስክከበር፥  መልካም አስተዳደር እስክሠፍን፥ ሙስናና ሌብነት እስክጠፉና የሎቄ ሰማዕታትና መላው የሲዳማ ህዝን ፍትህ እስክያገኝ ድረስ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል። በመሆኑም የሎቄውን  እልቂት በተመለከተ የሲዳማ ኤጄቶ የሚከተለውን መግለጫ ሰጥቶአል።

  1. እነዚህ ወገኖቻችን አንግበው የወጡት የመላው የሲዳማ ህዝብ የማንነት ጥያቄ  የሆነው እራስን በራስ የማስተዳደርና ክልል የመሆን ጥያቄ በአስቸኳይ ህገመንግሥታዊ መልስ ይሰጥበት
  2. ገለልተኛ የሆነ የሎቄን ዕልቂት መርማሪ/አጣሪ ኮሚቴ በአስቸኳይ ተቋቁሞ ይህን ዘግናኝ ጭፍጨፋ  ያዘዙና የጭፍጨፋው አካል የሆኑ ግለሰቦችን አጣርቶ ወደ ሕግ ፊት ያቅርብ
  3. መንግሥት በዚህ ኢፊትሐዊ ድርጊት የተገደሉ ወገኖቻችን ቤተሰቦችንና መላውን የሲዳማ ህዝብ ይቅርታ ይጠይቅ፤ ለሟች ቤተሰቦችም አስፈላጊ ካሳ ይክፈል
  4. በዚህ ግፍ ምክንያት ለተለያዩ የአካል ጉዳት ለተዳረጉ፣ ያለፍትህ ለታሰሩና ለተሠቃዩ  ግለሰቦች ካሳ ይከፈላቸው

ድል ለጭቁኑ ለሲዳማ ህዝብ፤
የሎቄ ሰማዕታት የተሰውለትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ትግሉ ተጠናክሮ ይቀጥላል!

ኤጄቶ

ግንቦት 17 2010 ዓ/ም

ሐዋሳ