በሲዳማ አካባቢ ስላለዉ ወቅታዊ የሃገራችን ሁኔታን በተመለከተ ከሲዳማ ኤጀቶ የተሰጠ መግለጫ

በአገራችን ላላፉት ሀያ ሰባት ዓመታት በሕዝባችን ላይ ተጭኖ የነበረው ሥርዓት ለአገዛዝ እንድያመች በማሰብ በተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች መካከል ለዘመናት አብሮ የዘለቀውን የሕዝቦች ባህላዊ ማንነት፣ ወግና እምነቶች ላይ የተመሠረተውን አብሮ ተቻችሎና ተፈቃቅሮ የመኖር እሴቶችን ደረጃ በደረጃ በመናድ በተቃራኒው በሕዝቦች መካከል መጠራጠርን፣ ቅራኔንና የጥላቻ ዘመቻ በማካሄድና በማደራጀት የከረመ ሲሆን ህደቱንም ፍጹም ሰላማዊ ለማስመሰል በሚዲያ ፕሮፓጋንዳ በማካኸድ በሕዝቦች መካከል እጅግ የሠፋ ልዩነቶች እንድፈጠሩ ማድረጉ ይታወሳል። ለዚህም ማሳያ የሚሆኑ በአገራችን በተደጋጋሚ በሕዝቦች መካከል በተለያዩ ወቅቶች የተከሰቱ መጠነ ሰፊ ግጭቶችን ማንሳት ይቻላል። የቅርብ ጊዜን እንኳን ለአብነት ብናነሳ በሱማሌና በኦሮሚያ ክልል መካከል፣ በደቡብና በኦሮሚያ ክልልሎች መካከል፣ እንዲሁም በደቡብ ክልል ኮንሶና ደራሼ፣ በጋሞና በዎላይታ መካከል የተነሱ ግጭቶችን መጥቀስ ይቻላል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሁኑ ሰዓት በአገራችን ያ ሁሉ አልፎ፣ መንግሥት ስላለፈው ሁሉ ይቅርታ ጠይቆ የእርቅ፣ የሰላም፣ የመቻቻልና የአንድነትን አስፈላጊነት ተገንዝቦ ከሕዝቦች ጋር እየሠራ ባለበት፣ የመንግሥትን አካሄድ ያልወደዱ፣ በዚህም አካኸድ የተደራጀውን የዘረፋ ሰንሰሌታቸውን የሚያጡና “የቀን ጅቦች” ተብለው የተገለጹ አካላት ሆን ብለው የሰለጠኑ ቡድኖችን በማሰማራትና በደቡብ የሲዳማ ሕዝብ የሚያነሳውን ለዓመታት የዘለቀውን የራስ ክልል አስተዳደር ጥያቄ ከሚቃወሙ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት በሠሩት ቅንብር በሐዋሳ ከተማ ለዘመናት ስከበር የኖረውን የሲዳማን የፊቼ በዓል ተከትሎ በጥቂት በሲዳማና በዎላይታ ሕዝቦች ተወላጆች መካከል የከፋ ግጭት መከሰቱ ይታወሳል። ይህንን ተከትሎ ክቡር ጠቅላይ ሚንስቴር ዶ/ር አብይ አህመድ እስከ ስፍራው ድረስ በመሄድ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሁሉ ጋር ተወያይቶ ሁኔታውን አረጋግቶ መመለሱ የሚታወስ ስሆን፣ የቀን ጅቦች አሁንም የሲዳማ ሕዝብ ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት አለማቆማቸው እየታየ ይገኛል። የሲዳማ ወጣቶችን እያደኑ መግደልና ማሰር፣ ብሎም ማስፈራራቱን ቀጥለውበታል። በዚህ መንገድ የሲዳማን ሕዝብ ለጸብ ለማነሳሳትና፣ የዶ/ር አብይን የለውጥ ሕደት ለማስተጓጓል በትጋት እየሠሩ ይገኛሉ። ይህንን አስመልክቶ የሲዳማ ኤጄቶወች የሚከተለውን የአቋም መግለጫ ሰጥተዋል።

1. የሲዳማ ኤጄቶወች በተቀነባበረ ሴራ ሰለባ የሆኑት ወንድማማች ሕዝቦች መካከል በተፈጠረው ግጭት ለሞቱት፣ ለቆሰሉት፣ ንብረታቸው ለጠፋና ለተፈናቀሉ የሁለቱም ብሔር ወገኖቻችን የተሰማውን ጥልቅና መሪር ሀዘን እየገለጸ፣ ድርጊቱንም በጽኑ እያወገዘ የዚህ እኩይ ድርጊት ፈጻሚወች በአስቸኳይ ተጣርተው በህግ ፍት እንድቀርቡ እንድደርግ እየጠየቀ፣ የሚቀርቡበትን ህደት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ለማቀላጠፍ እንደሚሰራ ይገልጻል።

2. “የቀን ጅቦች” ዓላማ የሆነውን አገራችንን የማተራመስና የዶ/ር አብይን የለውጥ ህደት ለማደናቀፍ፣ እንዲሁም የሲዳማ ሕዝብን ለጸብ በማነሳሳት ሌላ ግጭት ለመቀስቀስ በደቡብ ክልል ጸጥታ ኃይሎች በንጹሐን የሲዳማ ተወላጆች ላይ እየተፈጸመ ያለው ሕገ ወጥ ግድያ፣ ድብደባ፣ እሥራት፣ ማስፈራራትና ዛቻ በአስቸኳይ እንድቆም በአንክሮ ይጠይቃል።

3. ማንኛውም ተጠርጣሪ ግለሰቦች ወንጀላቸው ተጣሪቶ ሕጋዊ ውሳኔ እስክያገኙ ድረስ የሕግ ከለላ እንደማድረግ፣ ተጠርጣሪ ተብለው የታፈሱት የሲዳማ ወጣቶች፣ በደቡብ የጸጥታ ኃይሎች በደል እየተፈጸመባቸው፣ እየተደበደቡ፣ እየተገርፉና እየተገደሉ ባለበት ሁኔታ የሲዳማ ዞን አመራሮች ዝምታ የሲዳማን ሕዝብ እያስቆጣና የሲዳማን ሕዝብ ትዕግስት እየተፈታተነ ስለሚገኝ የሚመለከታቸው የሲዳማ ዞን አመራሮች ቆምንለት ለሚሉት የሲዳማ ሕዝብ ሕጋዊ ከለላ እንድያደርጉ ጥሪውን ያስተላልፋል።

4. ሁለቱን የጉዳት ሰለባ የሆኑ ብሄረሰቦችን እንደመሣሪያ በመጠቀም የሚራገበው የፕሮፓጋንዳና በአንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያወች የሚወጡ ጽሁፎች ሃላፍነትና ሚዛናዊነት በጎደለ መልኩ ያልተጣራ መረጃ በማራገብ ሁለቱ ለዘመናት በፍቅር፣ በሠላምና በአንድነት በኖሩ ሕዝቦች መካከል የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ ትልቅ ጠባሳ የሚፈጥርና ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ የሚደረገውን የምርመራ ህደትንም የሚጎዳ ስሜታዊና ግብዝ አካኸድ ይዘው የሚጓዙ አንዳንድ ሚዲያወች፣ ሶሻል ሚድያ ተጠቃሚወችና ጸሀፍያን ከድርጊታቸው እንድቆጠቡ በአጽንኦት እየጠየቀ እስከአሁን ያለውንም በጽኑ ያወግዛል።

5. በሁለት ሠላማው ብሄረሰቦች መካከል ድንገት በተቀነባበረ ሴራ የተከሰተውን ድርጊት በመንግሥት፣ በተለያዩ ሚዲያወች፣ በአገር ሽማግሌዎች፣ የድርጊቱ ሰለባ በሆኑ የሁለቱ ብሄረሰብ አባላት፣ እየተገለጸ ባለበት ወቅት ጥቂት የዎላይታ ወንድሞቻችን ሲዳማንም ሆነ የወላይታን ሕዝብ ለዘመናት ስበድሉ የኖሩ ጥቂት ባለሥልጣናትንና ከሲዳማ ሕዝብና ከዎላይታ ሕዝብ ባሕል ፍጹም ባፈነገጠ መልኩ አስጸያፍ ድርጊት የፈጸሙትን ከሰፊው ሕዝብ ባልለየ መልኩ አጉልቶ በማሰማት የሁለቱም ሕዝቦች የጋራ የሆነውና በዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን የሲዳማ ዘመን መለወጫ ፍቼ ጨንባላላ በዓልን ለማጥፋት የሚደረገው ዘመቻ፣ እንዲሁም የሐዋሳ ከተማ የአስተዳደርና የባለቤትነት መብት የመሳሰሉ ጉዳዮችን በትልቅ መድረኮች ላይ በማጉላትና በተለይዩ ሚዲያወች የሕዝቦችን ያለፈውን የአብሮነት ታሪክና የወደፊት የመጭው ትውልድ እጣ ፈንታ ያላገናዘበ አስተያየት በመስጠት የሚደረግ ዘመቻ በአስቸኳይ እንድቆም በአጽኖት እየጠየቀ፤ ጉዳዩ የሚመለከትው የመንግሥት አካልና የበዓሉ ባለበት የሆነው የሲዳማ ሕዝብ እንዲሁም መላው የአገራችን ሕዝቦች ይህንን ድርግት እንድያወግዙ በአጽንኦት ይጠይቃል።

6. የሲዳማ ኤጄቶወች በሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል በተቀነባበረ ድርጊት አንዱ ሌላውን በመጉዳት፣ በመግደል፣ ንብረት በማቃጣል ወዘተ የተሳተፉ የሁለቱም ብሔረሰብ አባላት ይሁኑ ሌሎች ግለሰቦች ሁለቱንም ትልልቅ የደቡብ ብሄሮችማንነት፣ እሴት፣ ባህላዊ የአኗኗር ዜይቤ የማይወክሉ መሆናቸውን በጽኑ ያምናል። እነዚህ ጋጤወጦች በአስቸኳይ ተጣርተው በአፋጣኝ ለፍርድ ለማቅረብ ተመጣጣኝና አስተማሪ ቅጣት እንድሰጥ በአጽኖት ይጠይቃል።

7. የሲዳማ ኤጄቶወችና ሰፊው የሲዳማ ሕዝብ ያነሱት የሲዳማ ሕዝብ የክልል አስተዳደራዊ ጥያቄ ከዛሬ 12 ዓመት በፊት በአገሪቱ ሕግና ሕገመንግሥት መሠረት አስፈላጊውን መሥፈት አሟልቶ የቀረበ በመሆኑና የሲዳማ ሕዝብ ሐሳዋ ከተማ ያለው የባለቤትነት መብት በማንም አካል ልወሰን የማይችል በመሆኑ ማንም በዚህ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገባ በአጽኖት እየጠየቀ፣ ይህ ጉዳይ የሕግ ተፈጻምነት እስከሚያገኝ ድረስ በጽናት የሚታገል መሆኑ ይገልጻል፤ የኤጄቶ ትግልም ፍጹም ሠላማዊና ህገመንግሥታዊ መሠረት ያለው የሲዳማ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ መሆኑን በድጋሚ ያስታውቃል።

ሁለት ወንድማማች ሕዝቦችን ለማለያየት የሚደረግ ዘመቻ በአስቸኳይ ይቁም!!

ኤጄቶ
ሐዋሳ – ሲዳማ
ሰኔ 21 2010