የ2ተኛ ዙር ጋዶን በሰላም መጠናቀቅ አስመልክቶ ከኤጄቶ የተላለፈ መልእክትና ምስጋና

የሲዳማን ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄን ተከትሎ ጥይቄው ህጋዊ መንገዱን ጠብቆ በመሄድ ላይ ይገኛል። በመሆኑም በተለያዩ ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነቶች እየተስተጓጎለና እየተጓተተ መሆኑን ተከትሎ የሲዳማ ኤጄቶ ሰላማዊ የትግል አዋጅ (ጋዶ) በማወጅ በጋዶ #1 በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ የተሳተፈበት በሀዋሳ ከተማ የተካሄደ ፍፁም ሰላማዊ የሆነ ሰልፍ በየካቲት 14/2011 መደረጉ ይታወሳል።

በዚህም የኢትዮጵያ መንግስት ለህዝቡ ምላሽ ሳይሰጥ በመቆየቱ ጋዶ #2 መታወጁ ይታወቃል፡፡ በዚህም የተመረጡ ተቋማትን የስራ ማቆም አድማ ከመጋቢት 4-6/2011 ጥሪ ተደርጎ እንደነበር ይታወቃል።ጥሪውን ተከትሎ በመላው የሲዳማ ምድር የተሳካ አድማ ተደርጓል። ለዚህም መሳካት መላው የሀዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ዞን ህዝብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ላለፉት በርካታ አመታት ደኢህዴን ህይወት እንዲኖረው የተደረገው በዋናነት በሲዳማ ህዝብ ላይ ጠላት በማብዛትና ሊሎች ብሄሮች በህዝባችን ጥያቄ ላይ ጥርጣሬ እንዲኖራቸው በማድረግ እንደነበር ይታወቃል። ይህ በጠላት ጠንሳሽነት የተንሸዋረረ ምልከታ ሙሉ በሙሉ እንደማይሰራ በሀዋሳ ከተማ የሚኖሩ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች ከሲዳማ ህዝብ ጥያቄ ጋር በመሰለፍ ለሲዳማ ህዝብ ጠላቶች ግልጽ መልእክት አስተላልፈዋል።

ምስጋና

ጥያቄያችሁ ጥያቄያችን ነው ብላችሁ ሀዋሳን ጨምሮ በሲዳማ ወረዳ ከተሞች የምትገኙ ነዋሪዎች፣ ባንኮች፣ የመንግስት መ/ቤቶች፣ ከፍተኛ የት/ት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ኢንዱስትሪ ፓርክ ሠራተኞች በሙሉ፤ ምስጋናችሁ የሲዳማ ነፃነት ይሁን።

መልእክት

የሪፈረረንደም ቀን በቅርብ ተቆርጦ የማይነገር ከሆነ ይህ ሰላማዊ ትግል በቀጣይነት በመጠን እና በይዘት ሰፋ ባለ መልኩ ተቀጣጥሎ ይቀጥላል። ይህን ትግል ለመቀልበስና የትግሉን አቅጣጫ በማሳት የሲዳማን ህዝብ ትግል አጠልሽታችሁ ለመቀልበስ የታተራችሁ ሀይሎች ዛሬም በኤጄቶ ትጋትና በሲዳማ ህዝብ አጋሮች ጥረት ድባቅ ተመትችኋል። ከዚህ ሰዓት ጀምሮ ጋዶ#3 እስኪታወጅ ድረስ መላው ሲዳማ ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴ የሚመለስ ይሆናል።

የጋዶ #3 ዝግጅትም የተጠናቀቀ መሆኑን በአፅንኦት እናስገነዝባለን!!

ኤጄቶ
መጋቢት 6/2011 ዓ.ም
ሀዋሳ ሲዳማ ኢትዮጵያ