በወቅታዊ የትግል ሁኔታዎች ላይ የሲዳማ ኤጄቶ ያወጣው የአቋም መግለጫ

በዛሬው ዕለት ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ የሲዳማ ኤጄቶ በሀዋሳ ከተማ ባህል ማዕከል አዳራሽ በአጠቃላይ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በተለይም በሲዳማ ህዝብ የክልል ጥያቄ፣ በፀጥታ ጉዳዮች ላይ እና በቀጣይ የትግል አቅጣጫዎች ላይ ውይይት ያደረገ ሲሆን ከዚህ በታች የተገለፀውን የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል።
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
“በወቅታዊ የትግል ሁኔታዎች ላይ የሲዳማ ኤጄቶ ያወጣው የአቋም መግለጫ”
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
“ለሲዳማ የክልልነት ጥያቄ የሚታገል የመጨረሻው ትውልድ” በሚል መሪ ቃል ህጋዊና ሰላማዊ ትግል እያደረገ የሚገኘው መላው የሲዳማ ህዝብ ወይንም ኤጄቶ ከምን ጊዜውም በላይ አንድነቱን አጠናክሮ የትግሉን ፍሬ ለመሰብሰብ የቀረው እጅግ ጥቂት ጊዜ መሆኑ ይታወቃል።

ይህንን ሰላማዊ ትግል ይዘቱን ለመቀየር የተለያዩ ፖለቲካዊ ሴራዎች የተሞከሩ ቢሆንም ፅኑ አቋም በያዘውና የሲዳማ አንድነት ላይ በማይደራደረው ኤጄቶ ትግሉ አሁን የደረሰበት ደርሷል።

በመሆኑም ይህንን ትግል ከዳር ለማድረስ በምንተጋበት በዚህ ጊዜ ጠላት የተለያዩ የተስፋ መቁረጥ ሴራ ሙከራዎች በደኢህዴንና ተላላኪዎቻቸው እየተሞከረ መሆኑን ደርሰንበታል።
ስለሆነም የሲዳማ ኤጄቶ ትግሉን ለማስቀጠል የሚከተሉትን የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

1. ኤጄቶ የሲዳማን ህዝብ የዘመናት ጥያቄ ለአንዴና መጨረሻ ጊዜ እንዲመለስ ከየትኛውም ፀረ-ህዝብና ጨቋኝ አስተሳሰብ አራማጅ ኃይሎች ጋር እልህ አስጨራሽ ሰላማዊና ህገመንግስታዊ ትግል የሚያደርግ የመጨረሻው ትውልድ አካል እንጂ የመንግስት ወይንም የፓርቲ ጉዳዮች አስፈፃሚ ቡድን አይደለም።

ስለሆነም በስመ-ኤጄቶ ፀረ-ትግል ተልዕኮ በመውሰድ የህዝባችንን የዘመናት ትግል ዋጋ በማሳጣት ወደነበረበት ዘመናዊ የባርነት ዘመን ለመመለስ በሲዳማ ምድር የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችንም ሆነ ቡድኖች አጥብቀን የምንቃወም ሲሆን አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ ከተግባራቸው የምናስቆማቸው መሆኑን እናሳውቃለን።

ህብረተሰቡም እኩይ ተልዕኮ ከበስተጀርባ ይዘው ጠቃሚ የሚመስሉ በማር የተለወሱ መርዞች ሲቀርቡለት በተለመደ የማስተዋል ጥበቡ ለይቶ እንዲያወጣና እንዲያጋልጥ እንጠይቃለን።

2. ኤጄቶ ማለት በራሱ ለህዝብ ሁለንተናዊ ነፃነት በትጋት፣ በፅናትና በቁርጠኝነት ህግን ተከትሎ የሚገባውን የሚጠይቅና ለብዙሃን ጥቅም የራሱን ህይወት አሳልፎ እስከመስጠት የሚታገል እውነት ላይ የቆመ የህሊናው ባሪያ ማለት ነው።

ለግል ጥቅማጥቅም፣ ሀብትና ስልጣን የሚሮጥ፣ የራሱን ሰብዓዊና ህገመንግስታዊ መብት ለማስከበር የሌላውን የሚደፈጥጥ፣ ከመርህና እውነት ይልቅ በጊዜያዊና ግላዊ አጀንዳ ላይ ውድ ጊዜውን የሚያጠፋ ከንቱ ትውልድ አይደለም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚህ የትግል እንቅስቃሴ መሰረታዊ መርሁን ጠብቆ የህዝባችንን የዘመናት ትግል አሁን የደረሰበት ደረጃ ፍፁም ህጋዊ በሆነ መንገድ ለማምጣቱ መላው ዓለም ምስክር መሆኑ እየታወቀ ትግሉን ለማቀዝቀዝና የኤጄቶን ህልውና ለመፈታተን ኤጄቶን እንደሽፋን በመጠቀም ተራ የስርቆት ወንጀል የሚፈፅሙ ጥቂት ወጣቶችን መንግስት ሆን ብሎ እያየ እንዳላየ በመሆን ወንጀለኞችን እያበረታታ እንደሆነ ደርሰንበታል።

ስለሆነም በመላው ሲዳማ ምድር መንግስት በወንጀለኞች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ እያሳሰብን ሂደቱን በከፍተኛ ጥንቃቄ የምንከታተለው መሆኑን እናሳውቃለን። ይህ ካልሆነ ግን መንግስት ህግ ለማስከበር አቅም እንዳጣ በመቁጠር ኤጄቶ የመላው ሲዳማንና ሌሎች ነዋሪ ወንድም ዜጎች ደህንነት ለመጠበቅ የሚሰራ መሆኑን እናሳውቃለን።

3. ደጋግመን “ይህ ትውልድ ለሲዳማ ክልል ጥያቄ የሚታገል የመጨረሻው ትውልድ ነው” ስንል ከምራችን ነው።
ስለሆነም ላለፉት 8 ወራት ከህፃን እስከ አዋቂ፣ ከሴት እስከ ወንድ፣ ከአርሶአደር እስከ ምሁር አለምን ያስደመመ ሰላማዊ የትግል እንቅስቃሴ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ የቆየ መንግስት ሲዳማ ምላሹን ሳያገኝ ህገመንግስታዊ የጊዜ ገደብ ከተጠናቀቀ በራሱ ክልል ለማወጅ በሚዘጋጅበት በዚህ ባለቀ ጊዜ ለውይይት መጋበዝ ትግሉን ከማዘናጋትና ከማጨናገፍ የዘለለ ፋይዳ እንደማይኖረው ኤጄቶ በፅኑ ያምናል።
ባይሆን መንግስት ኢ-ፍትሃዊ የሆነውን ደቡብ የሚባለውን አደረጃጀት በማፍረስና በሀገሪቱ የፌደራሊዝም ስርዓት መልሶ በማደራጀት የቆዩ ህዝባዊ ጥያቄዎችን ቢመልስና ዘላቂ ሰላም ቢያሰፍን እንዲሁም የሪፎርሙ ዋና አካል በማድረግ ሪፎርሙን እውነተኛ እንዲያደርገው እንመክራለን።
ውይይት ማድረግ አለማድረግ የሚሉ የሀሳብ ልዮነቶችን የዓላማ ልዩነት በማስመሰል ህዝባችንን ለመከፋፈል የሚደረግ ማንኛውንም እንቅስቃሴ የምንቃወም መሆኑን እየገለፅን ገፍተው ትግሉን አደጋ ላይ ለመጣል የሚሯሯጡ ጥቂት ግለሰቦችን ግን የማንታገስ መሆኑን እንገልፃለን።

4. ቀጣይ የትግል አቅጣጫዎች ሁለት መጠቅለያ ላይ የተንጠለጠሉ መሆናቸው ግልፅ ነው። በተጀመረው ህገመንግስታዊ ሂደትን የተከተለ ሪፈረንደም አካሂዶ ውጤቱን ለህዝቡ ማሳወቅ ወይንም ደግሞ ህገመንግስታዊው የጊዜ ገደብ ሲጠናቀቅ የራስ አስተዳደር ክልል በማወጅ የፌደራል መንግሥቱን መቀላቀል ናቸው።
ሁለቱም የራሳቸውን ዝግጅት የሚፈልጉ ቢሆንም የሚቀድመውን እያስቀደምን ለሁለቱም የምናደርገውን ዝግጅት አፋጥነን የምንገፋ ሲሆን ለዚህም
ሀ. ህገመንግስታዊ የማስፈፀም ስልጣን የተሰጠው የክልሉ ም/ቤት እንዲሁም የመፈፀም ግዴታ ያለበት ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ቀሪ ጊዜውን በአግባቡ በመጠቀም ተግባራቸውን ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ እንዲፈፅሙ አጥብቀን እንጠይቃለን።
ይህ ካልተፈፀመ ጋዶ 4 በቅርብ ጊዜ የምናውጅ መሆኑን ከወዲሁ እናሳውቃለን።
ለ. በሌላ በኩል ክልልን ህገመንግስታዊ በሆነ መንገድ ለማወጅ ዝግጅት እንዲያደርግ ኃላፊነት የተሰጠው የክልል ዝግጅት ሴክሬታሪያት የደረሰበትን ለህዝብ በተከታታይ በማሳወቅ በየደረጃው ህዝባዊ ውይይቶች በአስቸኳይ መጀመር እንዳለበት አጥብቀን እንጠይቃለን።

ሚያዝያ 23/2011 ዓ.ም
ኤጄቶ
ሀዋሳ ሲዳማ ኢትዮጵያ