በመላው ዓለም የሚኖሩ የሲዳማ ተወላጆች በግንቦት 16 1994 ዓ.ም በሐዋሳ ከተማ ልዩ ስሙ ሎቄ በሚባል አካባቢ የተጨፈጨፉ የሲዳማ ተወላጆችን ለ17ተኛ ጊዜ አስመልክቶ የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

የሲዳማ ሕዝብ ለበርካታ ዓመታት ለነጻነት እና እኩልነት በሚያደርገው ትግል ምክንያት ሲታሰር፣ ሲገደል፣ሲሰደድ፣ሲጨቆንና፣መብቱ ሲገፈፍ ኖሯል። ሕዝቡ ከአጼዎቹ ስርዓት ጀምሮ እስከ አሁኑ አገዛዝ ድረስ መራርና እልህ አስጨራሽ ትግል ማድረጉና እስከ አሁንም እያደረገ መሆኑ ይታወቃል። በመሆኑም የሲዳማ ሕዝብ እራሱን በራሱ ለማስተዳደር የጀመረው ትግል ሰሞነኛ ሳይሆን የቆየና በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑ በታሪክ መዛግብት ላይ ሰፍሮ ይገኛል። ይህንንም ትግል በየዘመኑ ያስተባበሩና የመሩ፣ በሂደቱም ውድ ዋጋ የከፈሉ የሕዝቡ የታሪክ ጀግኖች በመሆናቸው በሕዝቡ ዘንድ ለዘመናት ሲታወሱ ይኖራሉ። እነዚህ ጀግኖች ለሲዳማ ነጻነት ካደረጉት ትግል ባሻገር ለአገራችን ነጻነት ያበረከቱት አስተዋጽኦም ቀላል የሚባል አይደለም።

በደርግ ዘመነ መንግስት ወቅትም ነፃነት ናፋቂው የሲዳማ ሕዝብ በተደራጀና በተቀናጀ መንገድ ከፍተኛ ትግል በማድረግ ለእኩልነት፣ለነጻነት እና ለፍትህ ታግሎአል። በወቅቱ ሕዝቡን በማንቃት እና በማደራጀት ባደረገው ትግል የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ወይም ሲአን ለወታደራዊው መንግስት መንኮታኮት ከፍተኛ ድርሻ ከነበራቸው ጥቂት የብሄር ድርጅቶች መካከልም አንዱ ነበር። ድርጅቱ ለሕዝቦች እኩልነት ባደረገው ትግል የተመዘገበውን ውጤት መነሻ በማድረግ በሰላም ለመደራደር በ1983 ዓ. ም ትጥቁን በመፍታት አገር ቤት ቢገባም መንግስት ባደረገው ሸፍጥ ሕዝቡ የትግሉ ውጤት ተቋዳሽ እንዳይሆን ተደርጓል።

በመሆኑም ላለፉት ሀያ ስምንት ዓመታትም በአሁኑ አገዛዘ የሲዳማ ሕዝብ ለነጻነት፣ ለማንነት እና እኩልት ከፍተኛ ዋጋ ሲከፍል ቆይቷል። ከእነዚህ መስዋዕቶች አንዱ የሀዋሳው የሎቄ ጭፍጨፋ ነው፡፡ የቆየውን የህዝቡን በክልል የመደራጀት ጥያቄ እውን ለማድረግ መንግስትን በሰላማዊ መንገድ ለመጠየቅ ግንቦት 16 ቀን 1994 ዓ. ም ሰላማዊ ሰልፍ በወጡ የሲዳማ ተወላጆች ላይ የመንግስት ወታደሮች ባደረሱት ዘግናኝ ጭፍጨፋ ከመቶ በላይ የሚሆኑ ንጹሀን ወገኖቻችን ህይወታቸውን አጥተዋል። ይህን ጭፍጨፋ በወቅቱ የተለያዩ የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና ሚዲያዎች መዘገባቸውም ይታወሳል።

ከእነዚህ ተቋማት በላይ ግን ድርጊቱ በሁሉም የሲዳማ ተዎላጆች ልብ ተመዝግቦ ይገኛል፤ ዕለቱም በሲዳማ ሕዝብ ታሪክ እጅግ አሰቃቂና ጥቁር ቀን በመሆን በታላቅ ሀዘን በየአመቱ ታስቦ ይውላል። የሲዳማ ሕዝብ ዛሬም ቢሆን እራሱን በራሱ ለማስተዳደር በሚያደርገው የትግል ጉዞ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለ ይገኛል። በቅርቡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሲዳማ ተወላጆች በሰላማዊ መንገድ ድምጻቸውን ማሰማታቸው የሚታወቅ ቢሆንም ፤ መንግስት ሕዝብን ባለማክበርና እውቅናን ባለመስጠት እንዲሁም ህግ ን ባለማክበር በሠላማዊ ትግላችን ላይ ብቻ ሳይሆን በሕዝባችን ላይም ያለውን ንቀት በሚገባ በድጋሚ አሳይቷል። ከዚሁ ጋር በተያያዘና የሎቄውን እልቂት መታሰቢያ ምክንያት በማድረግ በውጪ የሚኖሩ የሲዳማ ተወላጆች ማህበር የሚከተለውን ባለ ስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

1ኛ. የሲዳማ ሕዝብ የትግል ዋነኛ መነሻ በሀገራችን የነበሩ መንግስታት ህግን ባለማክበራቸው እና ሰብአዊ መብትን በመጣሳቸው የተፈጸሙ የማንነት በደሎች መሆኑን ህዝባችን በጽኑ ያምናል። የአሁኑም መንግስት የህጎች የበላይ የሆነውን ህገ መንግስት ላለፉት ሀያ ስምንት ዓመታት ባለማክበሩ የህዝባችን እልቂት ዋነኛ መነሻ ሆኗል። ስለዚህ መንግስት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ህገ መንግስቱን እንዲያከብር በአጽዕኖት እናስገነዝባለን። የህዝቦችን እኩልነት እና አንድነት ለመሸርሽር ታስበው ከህገመንግስቱ ተጻረው የሚወጡ አዋጆች እና የፓለቲካ ትዕዛዞችንም አጥብቀን እንቃወማለን፡፡

2ኛ.ህገ መንግስታዊ የሆነውን በክልል የመደራጀት ጥያቄ በሰላማዊ ሰልፍ ለማቅረብ በወጣው ህዝብ ላይ ግንቦት 16 ,1994 ዓ.ም በመንግስት ወታደሮች በተፈጸመ ጭፍጭፋ ከ70 በላይ ንጹህን የሲዳማ ተወላጆች ውድ ህይወታቸውን አጥቷል፡፡ ቤተሰቦቻቸው ተፈናቅሏል፣የሞራል እና የንብረት ውድመት ደርሶባቸዋል። እንዲሁም በርካታ የቤተሰብ ጧሪ ልጆች፣ አባት ፣እናት፣ ወንድም ፣እህት ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ከስራ አለም ጨርሶ ተሰናብተው ለጎዳና ሕይወት ተዳርጓል። ስለዚህ መንግስት የሰብአዊ መብት ጥሰት መሆኑን ተቀብሎ ለእነዚህ ቤተሰቦች በአስቸኳይ የመቋቋሚያ ካሳ እንዲከፍል አጥብቀን እንጠይቃለን።

3ኛ.በሎቄ ጭፍጨፋ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ አመራር በመስጠት፣ በማስፈጸም እንዲሁም ድርጊቱን የተቃወሙ አካላትን በማስፈራራት ፣በማሰርና በማሳደድ ወንጀል የፈፀሙትን ግለሰቦች በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲያቀርብ እንጠይቃለን። ከዚህ በተጨማሪ በህዝባችን ደም እጃቸው የጨቀዩ ግለሰቦችን ዛሬም ቢሆን መንግስት ከአንድ ስልጣን ወደሌላኛው እያሻገረ እየሾማቸው እና እየሸለማቸው የመሄዱ እውነታ ህዝባችንን ያስቆጣ እና መንግስት በህዝባችን ላይ ሲፈጽም የቆየውን ድርጊት መቀጠሉን አመላካች ነው፡፡ ስለሆንም መንግስት በሲዳማ ውድ ልጆች ደም መጫወቱን በማቆም ድርጊቱ እንዳይደገም በሚያስተምር መንገድ ተግባራዊ እርምጃ እንዲወስድ እናሳስባለን፡፡

4ኛ.መንግስት የዜጎችን መብት መጠበቅና ማስተማር እንዲሁም መደገፍ ሲገባው የሲዳማ ህዝብ መብቱን ለመጠየቅ በሰላማዊ መንገድ ላደረገው እንቅስቃሴ እውቅና ከመስጠት ይልቅ የግድያ ፣የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፣ያለአግባብ እስራትና ስደት ህዝባችንን በመዳረጉ፣ አሁንም ቢሆን ይሄው በመቀጠሉ ፣ለሰላማዊ ጥያቄም እውቅናን በመከልከል ሰላማዊ ትግሉን በማንቋሸሽና በማጣጣል የሚያደርገውን ንቀት በመገንዘብ በግልጽ ቋንቋ ህዝቡን ይቅርታ እንዲጠይቅና የመብት ጥያቄውን እንዲመልስ አጥብቀን እናሳስባለን፡፡

5ኛ. በህዝባችን ላይ የተፈጸመ የሎቄ የጅምላ ጭፍጨፋ ዳግም በህዝባችንም ሆነ በሰው ዘር እንዳይፈፀም በጽናት ከህዝባችን ጎን በመሆን የምንታገል ሲሆን ህዝባችን ለትግል የከፈለውን ዋጋ እና የህዝባዊ ትግሉን ዓላማና ግብ ከግምት በማስገባት መንግስት ህዝቡ ለሚያነሳችው ጥያቄ ፍትሃዊ መልስ በአስቸኳይ እንዲመልስ እንጠይቃለን። ያለ አግባብ የተጨፈጨፉ ወገኖቻችንም እንዲታወሱ እና ድርጊቱ እንዳይደገም ለትምህርት በሚሆን መንገድ የመታሰቢያ ሀውልት እንዲቆምላቸው ሁኔታዎች እንዲመቻቹ እንጠይቃለን።

6ኛ. የሲዳማ ህዝብ በሚያደርገው ትግል እንዲሁም በህዝባችን አብሮነትና አቃፊነት ባህል ላይ መንግስት ህግን ባለማክበር እና ባለመፈጸም ለጸረ-ሕብረብሄራዊ-ፌደራልዚም ኃይሎች የሚሰጠውን ድጋፍ እንዲያቆም አበክረን እንጠይቃለን። በአሁኑ ጊዜም ያለአግባብ እየታሰሩ እና ዋጋ እየከፈሉ ያሉ ወገኖቻችንን ድምጽ በመስማት ድርጊቱንም በአስቸኳይ እዲያቆም በአጽንኦት እንጠይቃለን። ከዚህ ጋር በተያያዘ ህዝቡን በሥነልቦና ውጥረት ውስጥ ለመክተት ከአቅም በላይ ባልሆነ ችግር የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በሲዳማ ከተሞች በተለይም በሀዋሳ ለማስፈር የሚደረገውን አላስፈላጊ እንቅስቃሴ አጥብቀን እየተቃወምን የመከላከያ ሠራዊቱ ከአካባቢው በአስቸኳይ ለቆ እንድወጣ እንጠይቃለን።

በውጪ ዓለማት የሚኖሩ የሲዳማ ተወላጆች ማህበር ግንቦት 10,2011