በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከሲዳማ ኤጄቶ የተሰጠ መግለጫ

በቀጣይ የትግል አቅጣጫ ላይ በዛሬው ዕለት በሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ውይይት ያደረገው ኤጄቶ በዛሬው ዕለት የሚከተለውን መግለጫ አውጥቷል።

1. የሲዳማ ህዝብ አንድነት እና ለትግሉ ያለው ቁርጠኝነት ከመቼውም ግዜ በላይ የጠነከረበት ነው። በግል ፍላጎቶች በተናጡ ጥቂት ቅጥረኞች አማካኝነት አንድነታችን እንደተሸረሸረ ለማስደለቅ ለየት ያለ ሴራ ሲወጠን እንደ ነበር ደርሰንበታል። በዚህ ተራ ህልም የተነሳ የሚከስም ጥያቄ እንደሌለን የትኛውም ውጫዊም ይሁን ውስጣዊ ሀይል ሊገነዘበው ይገባል፡፡

በትክክለኛ ህዝባዊ የሀሳብ ፍጭቶችና ጥያቄዎች መካከል ተቆርቋሪ መስለው በገቡ ሰርጎ ገብ ፖጉማዎችና ተላላኪዎቻቸው የተጀመረ ትግል እንደሌለ ሁሉ የሚከሽፍ ትግል ባለመኖሩ አንድነታችንን ለማናጋት ለሚታትሩ ጥቂት ተለይተው ለሚታወቁ “ወገኖች” በመጨረሻ ሰዓት የመጨረሻ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ማስተላለፍ ይፈልጋል፣

2. በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ የግልፅነትና የመብት ጥያቄዎች ተገቢና ጠያቂ ዜጋ እንዲፈጠር ከታገልንባቸው ዓላማዎች ውስጥ ዋነኛው በመሆኑ በሚመለከተው አካል እውቅና ተሰጥቷቸው በአግባቡና በመንገዱ ግልፅነት መፍጠርና መመለስ የሚገባቸው በመሆኑ በጥቂት ፖጉማዎች ምክኒያት ህዝባዊ ፍረጃዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ መልዕክት ተላልፏል። ይህንን ተላልፎ ደምና አጥንት የተከፈለበትን ትግል ለማኮላሸት ለሚሞክር ለሱ ወዮለት!!

3. ክልል ለማወጅ ጥቂት ቀናት በቀሩን በዚህ ጊዜ ብዙ የቤት ስራ አለንና በዚህ ጊዜ ቅንጣት የአተያይም ሆነ የተግባር ስህተቶች ዋጋ የሚያስከፍሉ በመሆናቸው በቀላሉ የሚታለፉ አይሆኑም። በመሆኑም እስከመጨረሻው ሰዓት ሰላማዊና ህጋዊ ትግላችንን እስከ ደም ጠብታ በተቀመረ አኳዃን የምንቀጥል ይሆናል!!

4. ደኢህዴንም ሆነ የፌደራል መንግስት የህዝባችንን ሰላማዊና ህጋዊ ትግል መልክ ለመቀየር ከማሴር ይልቅ ራሳቸውን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ሰላማዊ የሽግግር መፍትሄ በማበጀት ለህዝባችን ደህንነትም ሆነ ለራሳቸው ህልውና እንዲሰሩ እናሳስባለን።

በመጨረሻም አንድ መርዶ ለጠላቶቻችን እናረዳቸዋለን! ሲዳማ ለብዙ ዓመታት እንዲፈርስ የተሰራበት አንድነቱን በዚህ አጭር ወራት በማይናድ መሰረት ላይ የገነባ በመሆኑ ደጋግማችሁ ሞክራችሁ እንዳጣችሁት ሁሉ መቼም እንደማይሳካላችሁ ነው!!!

ሰላም ለህዝባችን! ሰላም ለሀገራችን!
ኤጄቶ
15/10/2011 አ/ም
ሀዋሳ – ሲዳማ – ኢትዮጵያ