የሲዳማ ዳያስፖራ ማህበር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሰጠው መግለጫ!

የሲዳማ ሕዝብ በህገ መንግስቱ የተደነገገውን ራስን በራስ የማስተዳደር የመብት ጥያቄ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ መጠየቁ ይታወሳል። ይሁን እንጂ መንግስት ለሕዝባዊ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በተለያዩ መንገዶች ጥያቄውን ለመቀልበስ ጥረት ስያደርግ ቆይቷል። የሕዝቡን ሰላማዊ አካሄድ ችላ በማለት የሲዳማን ሕዝብ ከሌላው ወገን ለመነጠል በማሰብ የፕሮፓጋንዳ ስራ ስሰራና ተመሳሳይ ስራ የሚሰሩ አካላትን ስያበረታታ ኖሯል። የሲዳማ ሕዝብ ጥያቄውን በመጠየቁ ብቻ የሚደረስበትን በደል፣ ዛቻ፣ ማስፈራርያ፣ ታሪክ ማጠልሸት እና፣ የአንድነት አፍራሽ ተደርጎ እንዲታይ መደረጉ እንዲቆምና ከሚደርስበት ጥቃት ከለላ እንዲደረግለት ሕዝቡ በተደጋጋሚ ለመንግስት አቤቱታ ስያሰማ ሰነባብቷል። ሆኖም ግን መንግስት ዝምታ ከመምረጡም ባሻገር ምርጫ ቦርድና መንግስታዊ ሚድያዎች ድርጊቶቹን የበለጠ ስያስተጋቡ እንዲሁም መንግስት በፖርላማ በገዛ ሕዝቡ ላይ ይፋዊ ጦርነት ስያውጅ ተደምጧል። ይህንን ተከትሎ መንግስት በዛቻው መሰረት የሲዳማን ሕዝብ በጦር ወረራ እንዲደመስስ፣ የለውጥ ሀይል የሆነውን ወጣት ከማወያየት ይልቅ ባልሰሩት ወንጀል እንዲከስና፣ ከምድር እንድያጠፋላቸው የሚማጸኑ አከላትም ተስተውሎዋል።

መንግስት ለሕዝብ ጥያቄ ተገብውን ምላሽ ለመስጠት የማይቻልባቸውን ሁኔታዎች በዝርዝር ከሕዝቡ ጋር ከመወያየት ይልቅ የእነዚህን ሀይሎች ምክር ተግባራዊ ለማድረግ በቆረጠው መሰረት በወቅቱ ከምርጫ ቦርድ የተሰጠው ግልጽ ያልሆነ መግለጫ እና የህገ መንግስታዊ ጊዜ ገደብ በመጠናቀቁ ምን መደረግ እንደሚገባው ለመነጋገር ወደ ሕዝብ መሰሰብያ ስፍራ ጉዱማሌ በሚያመራው ህዝብ ላይ ወታደሮች በከፈቱት የተኩስ እሩምታ እና ይህንን ተከትሎ በተነሳው አለመረጋጋት መንግስት ባልታጠቀና ሰላማዊ የሲዳማ ህዝብ ላይ በወሰደው ወታደራዊ እርምጃ በርካታ ዜጎች ለሞት፣ለአካል ጉዳት፣ ለንብረት ውድመት ተዳርገዋል። እነዚህ ጉድዳዮችን አስመልክቶ በጁላይ 27/2019 ዓ .ም አስቸኳይ ስብሰባ ያደረገው በውጪ የሚኖሩ የሲዳማ ተወጅ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ማህበር የሚከተለውን ባለ አምስት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

1. ሰላማዊ የመብት ጥያቄ ባነሱ ሰላማዊ የሲዳማ ብሄር ተወላጆች ላይ መንግስት የወሰደውን ወታደራዊ እርምጃ በጽኑ እናወግዛለን። በጥቃቱም ውድ ህይወታቸውን፣ አካላቸውንና ንብረታቸውን ላጡ ዜጎቻችን፤ እዲሁም ያለ ወንጀላቸው ታስረው ለምንገላቱ ወገኖቻችን እና ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እንገልጻለን። ለዚህ ሁሉ ድርጊት ከመነሻው እስከመጨረሻው መንግስት እና የህዝብ ሰላማዊ የመብት ጥያቄ እንዳይመለስ በህዝብ ላይ የሀይል እርምጃው እንዲቀጥል ይወተውቱ የነበሩ አካላት ሙሉ ሀላፊነት ይወስዳሉ። የደረሰው ጉዳትም በገለልተኛ አካል ተጣርቶ በዝርዝር ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ አጥብቀን እንጠይቃለን።

2. መንግስት የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብት በመደፍጠጥ በመላው ሲዳማ ዞን የኢንቴርኔት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ በመዝጋት፣ ብቸኛ የህዝብ ሚድያ የሆነውን የሲዳማ ተሌቪዢን በመዝጋትና የጣቢያውን የስራ ሀላፊወች በማሰር፣ የመብራት አገልግሎት በማቋረጥ ሕዝቡን በጨላማ በመከላከያ ሰራዊት እንዲጨፈጨፍ ያደረገውን እኩይ አረመኔያዊ ተግባር በጽኑ እናወግዛለን። የአገራችን ሕዝቦች በሲዳማ ዞን ስለተከሰተው ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃ ማግኘት እንዲችሉ የሲዳማ ሚድያ ኔትወርክ ቴሌቪዢን ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ እንዲገባ፣ የታሰሩ የጣቢያው ሀላፊወች በአስቸኳይ እንዲፈቱና ገለልተኛ የሆኑ ሚዲያዎችና ተቋማት በነጻነት ገብተው ስለሁኔታው እንዲረዱ በአስቸኳይ ሁኔታወች እንዲመቻቹ አጥብቀን እንጠይቃለን።

3. የሕዝቡን ጥያቄ በሰላማዊ እና በሰለጠነ መንገድ ስያስተጋቡ የቆዩ ምሁራንን ከመደበኛ ስራ ገበታቸው ላይ በማፈናቀል ውሎ አዳራቸው እስር ቤት እንዲሆን የተደረገበት ነውረኛ የመንግስት ተግባር አጥቀን እናወግዛለን። ይህ ድርጊት የአገራችንን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እርባነ ቢስ የሚያደርግ፣ የሕዝቡን የመኖር ዋስትና የሚያሳጣ፣ ወጣቱ ለአገር ግንባታ ያለውን ፍላጎት የሚያኮስስ የመንግስት የጨለማ ጉዞ አካሄድ ፍንቱዊ አድርጎ የሚያሳይ በመሆኑ በጽኑ እናወግዛለን። ከሰላማዊ የህዝብ የመብት ጥያቄ ጋር በተገናኘ ያለወንጀላቸው ከህግ አግባብ ውጪ የታሰሩ ሁሉ በአስቸኳይ እንዲፈቱ አጥብቀን እናሳስባለን።

4. በሰላማዊ የሲዳማ ሕዝብ ላይ መንግስት በራሱ እና በጸረ ህዝባዊ ስርዓት ናፋቂ ሀይሎች በተቀነባበረ ግርግር የህዝብን ሰላማዊ ጥያቄ ለመደፍጠጥ በወሰደው የተሳሳተ እርምጃ በክሉሉ የታወጀው ወታደራዊ አገዛዝ በአስቸኳይ እንዲነሳ በአጽንኦት እየጠየቅን መንግስት መሰረታዊ የሕዝብ የመናገር፣ የመሰብሰብ፣ ሀሳብን በነፃ የመግለጽ መሰረታዊ መብት እንድጠብቅ እናሳስባላን።

5. ምርጫ ቦርድ በህግ ባልተሰጠው ስልጣን ጣልቃ በመግባት የሕዝቦችን ህገ መንግስታዊ የመብት ጥያቄ ከማደናቀፍ ተቆጥቦ ህዝበ ውሳኔ ለማካሄድ የሚጠበቅበትን የተክኒክ ድጋፍ ብቻ በአስቸኳይ እንዲሰጥ አጥብቀን እንጠይቃለን። ከዚህ በኋላ ሪፈረንደሙን በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ላለማካሄድ በምርጫ ቦርድም ሆነ በማንኛውም አካል የሚደረግ ማደናቀፍያ በሲዳማ ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የማይኖረው መሆኑን አጥብቀን እናሳውቃለን።

የሲዳማ ዳያስፖራ ማህበር

ከመላው ዓለም
ጁላይ 29፣ 2019