የኤሬቻን ምስጋና በኣል አስመልክቶ ከሲዳማ ኤጄቶች የተላለፈ የመልካም ምኞት መልእክት

የስርወ ገዳ ባህላዊ የሽግግር ሙዳይ ከሆኑት ትሩፋቶች አንዱ ኢሬቻ ነው። የኢሬቻ በኣል የኦሮሞ ብቻ ሳይሆን የኛ የሲዳማዎች ጭምር ነው። በኣሉ ከኛ ከኩሻውያን የተበረከተ ለመላው አለም የሚተርፍ የሰላምና የብርሃን ጮራ ነው።

በነዚህ የብርሃን ወራቶች ጽልመቶች ይገፈፋሉ ጥላቻና ሸፍጦች ይንበረከካሉ። በጭጋጋማውና ጥቁር ሰማይ የተከደነው የተፈጥሮ እውነት ያለ ከልካይ የሚገለጥበት ግዜ ነው። ኢሬቻ የዚህ ተፈጥሯዊ ኩነት ማሳያ ተምሳሌት ናት።

በዚህ በኣል ፈጣሪ ይመሰገናል፡ ፈጣሪ ደግሞ እውነት ነው።
እኛ ሲዳማዎችም ይህን ኡደት ሆላ ሃላሌሆ እንላለን። እውነት ታሸንፋለች። ብትቀጥን እንጂ አትበጠስም። የዘንድሮ በኣል የዚህ ማሳያ ነው።

የዚህን አመት አከባበር ከሌሎቹ ግዚያት ለየት የሚያደርገው የኦሮሞ ህዝብ ለሌሎች ጭቁን ህዝቦች ጭምር የተረፈ ደማቅ የትግል ምእራፍ ላይ በደረሰበት ማግስት መሆኑ ነው። ለዘመናት ተዘግቶ የከረመው የፍንፍኔ ሃርሰዲ ከዘመናት በኋላ ደግም ክፍት መደረጉ ለዚህ ድል፡ትልቅ ማሳያ ነው።

የኦሮሞ እና የሲዳማ ህዝቦች ለብዙ ዘመናት እውነት ተከደኖባቸው በባህላቸው እንዳይኮሩ በሃብታቸው እንዳይወስኑ ሲደረጉ የኖሩ ህዝቦች ናቸው። የዚህ ታሪክ ምእራፍ ግን ላይመለስ ሊከደን ግዜው የተቃረበ ይመስላል። አስቸጋሪው ክረምት አልፎ ደማቁ የኢረቻ ወር መጥቷል። ሀምሌ እና ነሃሴ ምንም ያህል ጽልመታሞች ቢሆኑ እንኳ መስከረምንና ህዳርን የመቋቋም አቅም አይኖራቸውም።

እኛ ሲዳማዎች ባለፉት ወራቶች በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከ100 በላይ ኤጄቶች ተገድለውብን የተቀሩት በእስር እንዲማቅቁ ተደርጎ ሌሎች በስደት እንዲንከራተቱ ሆኖ የክረምቱን ወራት አሳልፈናል። ይህም ሆኖ የመራራ ትግል ተምሳሌቶቻችን ከሆናችሁን ቄሮዎች ተምረን በብዙ ጽናትና ተስፋ ዛሬ ለኢሬቻ ወደ አደባባያችን ወጥተናል። ገድሎ ብቻ ሳይሆን ሞቶ ማሸነፍም እንደሚቻል የሰላምዊ አብዮት ጓዶቻችን(ቄሮች) አስተምረውናል። በዚህ መነሻ ዛሬ በሲዳማ መዲና በደማቅ ሁኔታ በሃዋሳ አክብረናል። በኣሉን ስናከብር ለአዲስ ትግልና መስዋእትነት ራሳችንን በማዘጋጀት ነው።

የቄሮና ኤጄቶ ትግል የእኔ ልብለጥ ትግል ሳይሆን የእኩልነት ትግል ነው። ይህንን እውነት ምድር የምትቀበልበት ግዜ እሩቅ አይደለም። እንደ አውሬ ስለው እና አስለው የጨፈጨፉን ጸረ ህብረ ብሄራዊነት ሀይሎች የእውነት ጸሀይ ስትወጣ ማፈራቸው አይቀርም። ውድ ኦሮሞ ወንድሞቻችን ቀጣዩ የምስጋና አመት ሌላ አዲስ ታሪክ ጽፋችሁ በአዲስ የትግል ምእራፍ የምትገለጡበት አመት እንዲሆን ምኞታችን ነው!!
ኤጄቶ
ሐዋሳ

ሲዱማ

ኢትዮጵያ